ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአዲስ አበባ ከተማ በ1922 ተወልደው ትምህርታቸውን በመጀመሪያ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፣ ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ሕንድ አገር ከሚገኘው ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ በባችለርስ ዲግሪ በመመረቅ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ ባገኙት ዕድል ወደ አሜሪካ አቅንተው ማሳቹሴትስ በሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በሥራው ዓለም በወጣትነታቸው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት በመምህርነት፣ ካርታ ሥራ ኢንስቲትዩት በካርታ ሥራ ሙያ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ቀጥሎም ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሚባለው በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሆነው ተቋም በመምህርነት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት መድረክ በመምህርነት ከተሰማሩት የዩኒቨርሲቲው ቀደምት ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሰሮች መካከል ይቆጠራሉ። በተለያየ ምክንያት ወዲያውኑ ባይጠሩበትም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሙሉ ፕሮፌሰርነትን አፅድቆ ያጎናፀፈው ለሳቸው ነበር።
ወጣቶችን ለማነፅ፣ እጅግ ብዛት ያላቸው ስብሰባዎች፣ ውይይቶች፣ ዝግጅቶች፣ ሥነፅሑፎችና መፅሐፎች ከማዘጋጀታቸውም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲቪክ ማሕበረሰቡ እንዲጎለብት፣ ሕዝብ የመደራጀት አቅሙን እንዲያበረታ፣ የአገሩንም መፃኤ ዕድል እንዲወስን ሲወተውቱ ኖረዋል። ዕድሜያቸውን በጥናታዊ ምርምርና በመምህርነት ሥራ ከመጠመድ ሌላ አገር የምታድግበትን፣ ወገን ከጭቆና የሚላቀቅበትን፣ ኑሮው የሚሻሻልበትን፣ መንግሥት ለሕዝብ ተገዥና ታዛዥ የሚሆንበትን፣ በጠቅላላው ሕዝብ የአገሩና የዕድሉ ባለቤት የሚሆንበትን መንገድ ራሱ ፈልጎ እንዲያገኝ ሲወተውቱና ሲጎተጉቱ፣ ከመንግሥት አካላትም፣ ከወገንም ጋር አብረው ሲወያዩና ሲያወያዩ፣ ሕዝብንም፣ መንግሥትንም ሲሞግቱ የኖሩ መምህርም፣ የሕዝብ ጠበቃም ነበሩ። ፅሑፎቻቸው “ውይይት” የሚባል በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚታተም መፅሔት ላይ ይገኙ ነበር። በተጨማሪም፣ በ1965 በአፍሪካ አዳራሽ የመሬት ይዞታን በሚመለከት “ገጠሪቱ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ያደረጉት ንግግር ከብዙ ሌሎች መካከል ተጠቃሽ ይሆናል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በሥራ ዘመናቸው ካበረከቷቸው እጅግ ብዙ መፅሐፍት መካከል ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር በመኪና፣ በእግርና በአህያ ሳይቀር አካልለው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያን የጂኦግራፊ መማሪያና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አትላስ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ፖሊሲዋ መሻሻል ተደርጎበት ገበሬው የራሱ ዕጣ ፈንታ ባለቤት እንዲሆን ሲሞግቱ ኖረው በስተመጨረሻም በሳቸው ጥናታዊ ሥራዎች አጋጣሚ የተጋለጠው ረሃብ አገራችንን የዓለም አቀፍ ዜና ርዕስ ሲያደርጋትና ከዚያም ተያይዞ በመጣው ለውጥ የሰዎች እልቂት በተለያየ መልኩ እየጨመረ አንጂ እየቀነሰ እንዳልመጣ የተረዱት ፕሮፌሰር መስፍን የእልቂቱ ሰበብ የሆነበት ምክንያት በየግዜው እየተቀያየረ አንድ ግዜ ረሃብ፣ አንድ ግዜ ጦርነት ወዘተ መሆኑ መሠረታዊ ጉዳዩን እንድንመለከት ያስገድደናል በማለት ትኩረታቸውን ወደ ሰብዓዊ መብቶች በማድረግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉን) በ1985 ከወዳጆቻቸውና ጉዳዩን ከሚረዱ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን መሠረቱ።
ኢሰመጉን ከመመሥረታቸው ከብዙ ዓመታት በፊት በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ከሌሎች ጋር በመሆን የመጀመሪያው የሲቪክ ማሕበር መሥራች ነበሩ። ይኸውም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበር ነበር። ለዚህም ዋጋ ከፍለዋል። በኢሕአዴግም ዘመን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)ን መሥርተው ሲያስተዳድሩ በተደጋጋሚ ለእሥር፣ ለወከባና ለእንግልት ቢዳረጉም፣ የሰብዓዊ መብት ውትወታና ሙግትን በሰፊው ተያይዘውት፣ ወጣት ባለሙያዎችን አሠልጥነው፣ ድርጅቱን አጠናክረውና ለዓለም አቀፍ እውቅና አብቅተው ወከባው ባይረግብም ለተተኪዎች ማቀበል በመቻላቸው የሲቪል ማህበረሰብ እንቅስቃሴ፣ ማለትም ሕዝብ የራሱን ዕጣ ፈንታ የሚያንፅበት፣ የአስተዳደርንም፣ የግል ኑሮውንም፣ የሃይማኖቱንም፣ የተለያዩ አገልግሎቶችና አቅርቦቶችንም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ በራሱ ተነሳሽነት የሚፈትሽበት፣ እንዳስፈላጊነቱም እርማትና መሻሻል እንዲደረግበት የሚወተውትበት ወይም በራሱ ተነሳሽነት እርማቱን የሚያድርግበት ባጠቃላይ የራሱ ዕድል ባለቤት የሚሆንበት ባሕልና አሠራር እንዲኖር የመጀመሪያውን አሻራ መጀመሪያ በሠራተኞች ማህበር፣ በኋላም በኢሰመጉ ትተው ሲያልፉ በነበራቸው ረጅም ዕድሜ በመደበኛ የትምህርት ተቋማት፣ በፖሊቲካ አደረጃጀቶች፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በሌሎች ስብስቦች ኢትዮጵያውያንን እየሰበሰቡና ባሉበት እየሄዱ አቅማቸውና የጤናቸው ሁኔታ ከሚፈቅደው በላይ የደከሙ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
ፕሮፌሰር መስፍን በምሑርነታቸው ካበረከቷቸው ሥራዎች መካከል ከላይ የተጠቀሱት አትላስና የጂኦግራፊ መፅሐፍት ቀደምቱ ቢሆኑም፣ ከነዚህ በኋላ እጅግ በርካታ መፅሐፍትን፣ ጥናታዊ ፅሑፎችን፣ ውይይቶችን፣ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት መድረኮች በማቅረብ ብዙ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
በተጨማሪ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥትን በፍራቻ ማየት እንዲያበቃና በሳቸው አነጋገር በሥልጡን መንገድ ሕዝብ ባለቤትነቱን እንዲያሳይ፣ ከጦርነትና ከግፍ አዙሪት እንድንወጣ ብዙ የጣሩ፣ ያንንም በማድረጋቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ፕሮፌሰር መስፍን በደርግ ዘመን የ10ኛውን አብዮት በዓል አያይዞ በተደረገው ዝግጅት ከውጭ ተጠርተው ከመጡ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ለአገልግሎት ዘመናቸው ሽልማት ሊበረከትላቸው እንደሆነ ሲነገራቸው ዕለቱን እቤታቸው አሳልፈዋል። በአንፃሩ በDefend Defenders የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅት በህዳር 2012 የሰጣቸውን ሽልማት በቦታው ተገኝተው በዘጠና ዓመት ዕድሜአቸው ሲቀበሉ የተናገሩት መንግሥታት ከሚሰጧቸው ሽልማት ከባልደረቦቻቸው የሚያገኙት ዕውቅና እንደሚበልጥባቸው የሚገልፅ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ዕድሜ ልካቸውን የምሑርነታቸውንና የጥናታዊ ምርምራቸውን የተለያዩ የሥራ ውጤቶች የአገሪቱን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት ግብዓት እንዲሆኑ ሲተጉ በመኖራቸው ሥራቸው በተለያየ የሙያ መድረኮች ዕውቅናን አግኝቷል። ለአብነት፣ እኤአ በ1994 የRobert F Kennedy Human Rights Award ተሸላሚ ለመሆን፣ እንዲሁም እኤአ በ2006 በአውሮፓ ሕብረት የአንድሬይ ሳካሮቭ መታሰቢያ የሰብዓዊ መብቶች ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በእጩነት ስማቸው ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በማስተርስ ዲግሪ የተመረቁበት የአሜሪካው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ በአገራችን በየግዜው ይከሰት የነበረውን ረሃብ ለማጥናትና የገበሬው ኑሮ የሚሻሻልበትን መንገድ ለመፈለግ ብዙ ዓመታት የፈጀ ጥናታቸውን ተመልክቶ እኤአ በ2003 የክብር ዶክቶሬት ሰጥቶአቸዋል። በተጨማሪም እኤአ በ2006 የNew York Academy of Sciences ዓመታዊውን Heinz Pagel Human Rights of Scientists Award ያበረከተው ለሳቸው ነበር።