ታላቁን የሰላም ሰው ስናስብ
(የፕ/ር መስፍን ወልደማርያም የተወለዱበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ከፋውንዴሽኑ የተሰጠ መግለጫ)
“ሰላምና የሰላም ትርጉም፣ የአንድ ወገን መሸነፍና መዋረድ፤ የሌላው ወገን ማሸነፍና የድል ሃሴት መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም፣ ሰላም የየትኛውም አይነት ልዩ ልዩ አመለካከቶች እንዳይኖሩ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ብቸኛው ሰላምና የሰላም ትርጉም ሊሆን የሚችለው፣ ኀይልንና አፍራሽ ግጭትን በአወንታዊና ገንቢ ድርጊቶች መለወጥ፤ በጥይት የሚደረግን ትግል በቃላትና በሃሳብ ፍጭት መቀየር፤ ፍርዱንም ለኢትዮጵያ ህዝብ መተው ማለት ነው።”

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በ1983 ዓ/ም በአስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ጥናት አለም አቀፍ ጉባኤ ካቀረቡት፤
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ሲታወሱ ለሰላምና ለሰው ልጆች መብቶች መከበር የሠሩት ሥራ ገዝፎ ይታያል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ጥብቅ አቅዋምም በማንም ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ረሃብንና ችጋርን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ፈጽሞ ለማቆራረጥ፣ ሀዝቡ የራሱ እድልና የስልጣን ባልቤት እንዲሆን የከፈሉት መሰዋዕትነት ሊዘነጋ የሚችል አይደለም፡፡ ለዘመናት የሰፈነው የጭቆና አገዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢያሰቃየውም ለፍትሕና ለሕግ የበላይነት ያለውን ጥልቅ እምነትና ጥማት መሰረት አድርገው በሕይወት ዘመናቸው ያደረጉት ትግልም ሲታወስ ይኖራል፡፡ በረዥሙ የትግል ሕይወታቸው የተከተሉት መንገድም ፍጹም ሰላማዊ እንደነብረ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋውንዴሽን፤ ዛሬ ሚያዚያ 16/2017 ዓ/ም የእኒህን ታላቅ የሰላም ሰው ዕለተ ልደት ሲያከብር፣ ከሁሉም ላቅ አድርጎ የሚያስታውሰው ይህን ለሰላም ያደረጉትን አስተዋጽኦ በአንክሮ በማሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትገኝበት አስቸጋሪ የሰላም ሁኔታም ፋውንዴሽኑ በጎላ ድምጽ የሰላምን መስፈን አስፈላጊንት እንዲያሳስብ ያስግድደዋል፡፡ ሰላምን በሰላማዊ መንገድና አሠራር ብቻ ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥረት ማድረግ ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ እንደሆነ ማሳሰብም ይፈልጋል፡፡ ዛሬ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል በሚካሄዱ ግጭቶች የሚያልፈው የሰው ሕይወት፣ የሚወድመው ንብረት ሁሉ ክሰላማዊው ሕዝብ ኑሮና ፍላጎት ጋር በምንም መንገድ የሚጣጣም አይደለም፤ ይህን እውነታ የትኛውም ወገን ልብ ሊለው እንደሚገባ ፋውንዴሽኑ ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡
ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ የማይፈልግ ሰው አለ ተብሎ አይገመትም፡፡ ሰላምን ለማግኘት ሕዝብ በየውሎው የሚያደርገው ብዙ ነው፣ ምእመናን በየሃይማኖት እምነታቸው ለሰላም ይጸልያሉ፣ ነጋዴው፣ ገበሬው፣ በየሥራ ዘርፉ የተሰማራው ለፍቶ አዳሪ ህዝብ ሁሉ ሰላምን ይፈልጋል፡፡ ጥያቄው ይህ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም የሚገኝበት መንገድ ወይም ብልሃት ምንድነው የሚለው ነው፡፡ የሰላም እጦት ምንጮች ብዙ ሊሆኑ ቢችሉም ሰላምን የማግኛ ዘዴው ግን አንድ እንደሆነ ፕ/ር መስፍን ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡ ሰላምን የማግኛ ብልሃቱ አንድ ብቻ ነው__ ሰላማዊና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት፣ ንግግር እና ክርክር እንደሆነ ደጋግመው ጽፈዋል፣ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ብቸኛ መንገድ መራመድ የምንጀምርው መቼ ነው?
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋውንዴሽን በስማቸው የሚጠራ ብቸኛና ህጋዊ ድርጅት ነው፤ ፋውንዴሽኑ የፕ/ር መስፍንን ልደት ሲያከብር ሁሉም ወገን ለሰላም በዚህ መንገድ መራመድ እንዲጀምር ጥሪ ያደርጋል፡፡ የፋውንዴሽኑ የተግባር ዐምዶች፣ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ፣ በህግ የበላይነት ጉዳይ፣ ረሃብን ከኢትዮጵያ በማስወገድ ሥራ እና ሰላምን ስለማስፈን መቀስቀስና ማስተማር ነው፡፡
የፕ/ር መስፍንን ሃሳቦችና ሥራዎች የምትወዱ፣ የምትደግፉና የምታራምዱ ስዎችና ቡድኖች ሁሉ፣ ፋውንዴሽኑ የእሳቸውን ሥራዎችና ስለእሳቸው የተሠሩ ስራዎችን አሰባስቦ በቅርስነት ለማቆየትና ለተከታታይ ትውልዶች ማስተማሪያ በሚሆን መልኩ ለሕዝብ እይታ የሚቀርብበትን ሁኔታ ከወዲሁ እያመቻቸ ይገኛል። ስለሆነም በእጃችሁ የሚገኙ የእሳቸውን ሥራዎች(መጻህፍት፣አጫጭርም ሆኑ ረዣዥም በጋዜጣና በመጽሄት የታተሙ ሥራዎቻቸው፣ቃለ ምልልሶችና የመሳስሉትን)፣ በሳቸው ዙሪያ የተሠሩ የትለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን(ስእል፣ቅርጻ ቅርጽ፣ ፎቶግራፍ የመሳስሉትን) ለፋውንዴሽኑ ድጋፍ እንድታበረክቱ በትህትና እንጠይቃለን። ይህ ሲደረግ የባለቤትነት መብታችሁ ሳይቀነስ በፈለጋችሁበት ጊዜ ሁሉ ፋውንዴሽኑ መልሶ ሊያቀርብላችሁ እያረጋገጠ ነው።
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሰላም በአንድነት እንሥራ!
ለፋውንዴሽኑ ከላይ እንደተገለጸው የተለያዩ የሥራ ፍሬዎችን ውይም የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ለምትፈልጉ
ስልክ ቁጥር_______________ +251956570106
ዌብ ስይት_______________________ http://mesfinwoldemariam.org
አቢሲኒያ ባንክ ሂሳብ ቁጥር________________ 58190993
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር______________ 1000564115401